September 17, 2025

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት አስተባባሪነት እና በስድስት የፌዴራል ተቋማት ተሳትፎ የማንሰራራት ቀን “ዘላቂ ልማት፣ ለሀገራዊ ማንሠራራት!” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች እና በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ በመንግስት የለሙ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ የልማት ፕሮጀክቶች ጉብኝት በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡

የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴርን ጨምሮ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ማዕድን ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር እና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በጋራ ባዘጋጁት ፕሮግራም ላይ የሚኒስቴር መ/ቤቶቹና የተጠሪ ተቋማት አመራርና ሠራተኞች እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ኃላፊዎች የታደሙበት ነው፡፡

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አዳራሽ የተካሄደውን መድረክ በይፋ ያስጀመሩት ክቡር አቶ አክሊሉ ታደሰ፣ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ላለፉት 14 ዓመታት ብዙ መውጣትና መውረድ የታየበትና የላብና የደም ዋጋ የተከፈለበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ በዛሬው ዕለት ለምረቃ በመብቃቱ ከተስፋ ወደሚጨበጥ ውጤት የበቃንበት ቀን ስለሆነ ድሉ የሁላችንም ነውና እንኳን ደስ ያለን ካሉ በኋላ በቀጣይ በመፍጠርና በመፍጠን ካሰብነው ጉዞ የማንመለስ፣ ድህነትና ኋላቀርነት የሰለቸን ህዝቦች ስለሆንን ካሰብነው የብልጽግና ግብ ለመድረስ በአንድነት እንቆማለን ብለዋል፡፡ አያይዘውም የህዳሴ ግድባችን ከብረት የጸና የትስስር ክንዳችን ስለሆነ ወደቀይ ባህር ለምናደርገው ጉዞ ከግማሽ በላይ የመደራደር አቅምን የፈጠረልን ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር፣ ኢ/ር) በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው ኢትዮጵያ የከፍታ ጉዞዋን እያረጋገጠች መሆኗን በመግለጽ በሚኒስቴር መ/ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተተከለውን ሶላር ፓናልና ሙዚየሙን ያስጎበኙ ሲሆን የኃይል አማራጭን፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃን፣ የተፋሰስ ልማትን፣ የሜትሮሎጂ ሣይንስን በስፋት ለመጠቀም እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል፡፡

በአዳራሹ የተካሄደው ሌላው ጉዳይ ዳግማዊ አድዋ! በሚል ርዕስ ጉባ ላይ እየተካሄደ ያለውን ክንውን የሚያስቃኝ የቀጥታ ስርጭት ለእይታ በቅቷል፡፡

በመስክ ጉብኝቱም ከእንጦጦ እስከ ኢሬቻ አደባባይ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት የተጎበኘ ሲሆን ይህን መርሃ ግብር የመሩት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሔለን ደበበ ሰው ሰራሽ ኩሬዎችን በመገንባት የአፈርና የውሃ ሃብታችንን ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አስተባባሪነት የኢትዮጵያ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጥገና ማዕከል የተጎበኘ ሲሆን ከጉብኝቱ በፊት በአየር መንገዱ የስራ ኃላፊዎች ስለአየር መንገዱ አጠቃላይ ገለጻ ተደርጎ ቢሾፍቱ ላይ የሚገነባውና ከ4 ዓመት በኋላ የሚጠናቀቀው አየር መንገድ በርካታ ዕድሎችን ይዞ የሚመጣና የአየር መንገዱን የከፍታ ጉዞ የሚያሳይ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ
የካሜራ ባለሙያ፡- አስመላሽ ተፈራ እና ፈዬ ደሜ

Posted in: News