
October 20, 2024
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 ዓ.ም ፡-(ከመልሚ) የከተማ መሬትን የመረጃ ሥርዓት በማዘመን ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ይህን የገለጹት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ ከሪፎርም በኋላ እየተገበራቸው የሚገኙትን ዘመናዊ አሠራሮችን አስመልክተው ባደረጉት ጉብኝት ነው፡፡
ክብርት ሚኒስትሯ ቢሮው ያከናወናቸውን ተግባራት እጅግ አድንቀው ሚኒስቴር መ/ቤቱ በቁሳቁስ ድጋፍ፣ በአቅም ግንባታ፣ ሊያሰሩ የሚችሉ የህግ ማዕቀፎችን ከጊዜው ጋር ሊሄዱ በሚያስችል መንገድ በማሻሻል በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ከተሞች በፈጣን ዕድገት እንዲጓዙ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
ለዚህም በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በኮሪደር ልማት እየተከናወኑ የሚገኙት ሥራዎች ማሳያ ናቸው ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ በተለይ የመሬት መረጃን ዲጂታላይዝ በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያከናወነው የሚገኘውን አሰራር ሌሎች ከተሞችም እንደተሞክሮ ወስደው ሊተገብሩት እንደምገባ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ እንደተናገሩት በኮሪደር ልማት ምክንያት ከይዞታቸው ለሚነሱ ዜጎች የመሬት መረጃቸውን ዲጂታላይዝ ማድረግ በመቻሉ ዜጎችን ከእንግልትና በአቋራጭ ለመበልጸግ ከሚሞክሩ ሌቦችና ደላላዎች መከላከል እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡
ቢሮዉ በዋናነት ያከናወናቸው ተግባራት የቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማት ግንባታ እና የተቋማት ኔት ወርክ ትስስር፣ መረጃን ዲጂታላይዝ በማድረግ የአስተዳደር ሥርዓትን መዘርጋቱ፣ የመሬት አገልግሎትን ወረቀት አልባ አስራር ማድረጉ፣ በርካታ የህግ ማዕቀፎችን ከአደረጃጀት ጋር ተግባራዊ ማድረጉ፣ ለተገልጋዮችም ሆነ ለሠራተኞች ምቹ የስራ አካባቢ በመፍጠር ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሠራርን ተግባራዊ በማድረግ አሠራሩን ማዘምን እንደቻለ በየደረጃው የሚገኙ የቢሮው ኃላፊዎች ለጎብኝዎች አብራርተዋል፡፡













