
August 13, 2025
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 1/2017 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)
በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ቁልፍ ችግር በአጭር ጊዜ በመፍታት አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት እንዲያስችል ታስቦ በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የተቋቋመውና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችንና የኢንዱስትሪውን ተዋናዮች በውስጡ ያቀፈው 9 ዓባላት ያሉት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ስትሪንግ ኮሚቴ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም ስራውን በይፋ መጀመሩ ይታወቃል፡፡
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሸቲቭ ስትሪንግ ኮሚቴ በተመሰረተበት ቀን ባደረገው ስብሰባ ላይ በስሩ 6 የስራ ቡድኖችን ያቋቋመ ሲሆን ያቋቋማቸው የስራ ቡድኖች በየራሳቸው የሰሯቸውን ስራዎችና የደረሱበትን ደረጃ የሚገመግም መድረክ በዛሬው ዕለት ቃሊቲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የስልጠና ማዕከል ውስጥ ተካሄዷል፡፡
በምስረታ መድረኩ ላይ ለተቋቋሙት የስራ ቡድኖች በተሰጡ አቅጣጫዎች መሠረት የተቋቋሙት የስራ ቡድኖች የሰሯቸውን ስራዎች የተመለከቱ ሪፖርቶች በየቡድኑ ሰብሳቢዎች እንዲቀርቡ ከተደረገ በኋላ የጋራ ውይይት ተደርጎ ቀጣይ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡
ስብሰባውን የመሩትና የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የስቲሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የመሠረተ-ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት ሲሆኑ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ ዮናስ አያሌው (ኢንጂነር) የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡
በመጨረሻም የስቲሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢው፣ ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሸቲቭ 2025-2050 ነሀሴ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የኢንዱስትሪው ቤተሰቦች በተገኙበት በስካይላይት ሆቴል ላውንች የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ
የካሜራ ባለሙያ፡- አስመላሽ ተፈራ