December 27, 2024

አዳማ፣ ታህሳስ 5/2017 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)

በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር በሥራ አመራር፣ በአሠራር ስርዓት፣ በዕቅድ አዘገጃጀትና አፈጻጸም ክትትል ስርዓቶች ላይ በማተኮር ለሚመለከታቸው የአስተዳደር ዘርፍ አመራርና ሠራተኞች የተዘጋጀ ግምገማ ነክ የስልጠና መድረክ በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ ተካሄደ፡፡

በስልጠና መድረኩ ላይ የተገኙት የሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ አባድር ፋሪስ በመክፈቻ ንግግራቸው የዚህ መድረክ መዘጋጀት ዋነኛ ዓላማ አመራሩ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት  በተለዩት የስራ ክፍሎች ተግባብቶና ተደጋግፎ በመስራት የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት ይቻል ዘንድ አሠራሩ መስመሩን ጠብቆ እንዲጓዝ ለማድረግ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን መቅረፍ በማስፈለጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሚቀርቡት ሠነዶች የተገኙ አበረታች ውጤቶችንና የታዩ ውስንነቶችን የለዩና ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችሉ በመሆናቸው በጋራ ተወያይቶ የጋራ አረዳድ መያዝ ስለሚያስፈልግ በሚቀርቡ ሰነዶች መነሻነት በጋራ ተወያይተን አቅማችንን እንድንገነባ እና እራሳችንን በመፈተሸ ከውይይት ጭብጦች በመነሳት ለቀጣይ አቅጣጫ የሚሆኑ ሀሳቦችን ለማመንጨት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቀረቡት የውይይት መነሻ ሠነዶች በሚኒስትርና በዘርፍ አማካሪዎች አማካኝነት ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኜ ልምድ፣ በስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ የቀረበው የአንድ ዕቅድና የአንድ ሪፖርት የአፈጻጸም ግምገማና ከክልሎች ጋር ስለሚዘጋጀው የዕቅድ መናበብ እንዲሁም የትግበራ አፈጻጸም የመረጃ ልውውጥ ጉዳይ እና በተቋማዊ ለውጥ ስራ አስፈጻሚ በኩል የቀረበው የለውጥ መሣሪያዎች አተገባበርን የተመለከተው ሠነድ ይገኙበታል፡፡

በተደረገው የጋራ ውይይት ከመረጃ አያያዝ አንጻር የታዩ ችግሮችና  በዕቅድ መናበብና በሪፖርት ቅብብሎሽ ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ረገድ የሚታዩ ችግሮችን መቅረፍ፤ የነበሩና የተቀዛቀዙ አሠራሮችን ማሻሻል፤ በዕቅድና በሪፖርት አዘገጃጀት ማኑዋሎች ላይ ያለንን ግንዛቤ ማሳደግ፤ ዕውቅናና ማበረታቻ የመስጠት ተሞክሮን መቀመር፤ የመረጃ አያያዝ ችግሮችን መቅረፍ፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማስፋት፤ አዳዲስ ኢኒሼቲቦችን ተቀብሎ ለመተግበር የሚያስችል አቅም መፍጠር፤ በጀትን ከውጤት ጋር ማስተሳሰር፤ ዋን ኦፊስን በተገቢ ሁኔታ መተግበር፤ የለውጥ መሣሪያዎችን ተግባር ላይ ማዋል የሚሉትና ሌሎች በግብኣትነት የሚያገለግሉ ተጨማሪ ሀሳቦች ተነስተዋል ፡፡ 

ውይይቱን የመሩት የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ባህሩ አሸኔ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት በሚኒስቴር መ/ቤቱ በተሞክሮነት የሚወሰዱ ጠንካራ የአሠራር ስርዓቶች እንዳሉና በአፈጻጸም ረገድ በሚፈለገው ልክ ያልተሄደባቸውን በመለየት ረገድ የቀረቡት ሠነዶችና ከቤቱ የተሰጡ አስያየቶች ያሉብንን ችግሮች  ያሳዩ በመሆናቸው አብዛኛውን ነገር ተቀብለን የምንተገብራቸው ይሆናል ብለዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ
የካሜራ ባለሙያ፡- ፈዬ ደሜ

Posted in: News