
February 24, 2025
(የካቲት 09/2017 ዓ.ም ) የዲላ ከተማ መንግሥት ኮሙኒኬሽን
በጌዴኦ ዞን የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ስራዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢፌዴሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ የትምጌታ አስራት ገልጸዋል ።
በሚኒስትር ደኤታው አቶ የትምጌታ አስራት የተመራው የሱፐርቪዥን ቡድን በዞኑ በተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል ።
የሱፐርቪዥን ቡድኑን የሚመሩት አቶ የትምጌታ አስራት ሚንስቴር መስሪያቤቱ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በሚገኙ ከተሞች ቡድኑ በማዋቀር የድጋፍና ክትትል ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል ።
እንደ ሀገር በከተሞች ሪፎርም ተደርጐ ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ እንደሚገኝ የገለጹት ሚንስትር ደኤታው አቶ የትምጌታ ይህንን አጠናክሮ በማስቀጠል በዞን የሚገኙ ከተሞችን ከዚህም በላይ ለማልማት በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ።
በዞኑ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ስራዎች ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቁ ለማድረግ ሚኒስትር መስሪያቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ የትምጌታ አረጋግጠዋል ።
የጌዴኦ ዞን ም/አስተዳደርና የግብርና መምሪያ ኃላፊ ታጠቅ ዶሪ (ዶ/ር) የኢፌዴሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በዞኑ የሱፐርቪዥን ስራ ለማከናወን በመምጣታቸው አመስግነዋል ።
በሚኒስቴር መስሪያቤት አማካኝነት የሚከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎች በተለይም የቡሌ ሀሮ ዋጩ መንገድ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ትኩረት እንዲሰጥ ሀላፊው ጠይቀዋል ።
የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሽፈራው በበኩላቸው የዲላ ከተማ በራሱ አቅም እና በማህበረሰብ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመሰረተ ልማት ስራዎች የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
አቶ ዳንኤል አክለውም ከተማ አስተዳደሩ በኮርደር ልማት እና በሌሎችም ፕሮጀክቶች እያደረገ ያለውን ጥረት የፌዴራል መንግስት እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል ።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በዞኑ በመንገድ ግንባታ ፣ በውሃ ዝርጋታ ፣ በድልድይ ስራ ፣ በኮርደር ልማት ፣ በካሳ ክፍያ እና በሌሎች ፕሮጀክቶች የሚታዩ ክፍተቶችን ለሚኒስትር መስሪያቤት ጥያቄ አቅርበው ማብራሪያ ተሰጥቷል ።
በመጨረሻም በዳላ ከተማ የተሠሩ የልማት ስራዎች ተጎብኝተዋል።የዲላ ከተማ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን።