March 5, 2025

ቢሸፍቱ፣ የካቲት 25/2017 ዓ.ም፡- (ከ.መ.ል.ሚ) የገጠር መንገድ ትስስር ተግባራዊ በማድረግ  የምግብ ዋስትናን በሚፈለገው ልክ ማረጋገጥ እንደሚቻል ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው ከሁሉም ክልሎች ለተውጣጡ የመንገድ ዘርፍ የስራ ኃላፊዎች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ነው፡፡

መድረኩ በሚኒስቴር መ/ቤቱ እና በኮንስትራክሽን ማኔጅሜንት ኢንስትቲዩት አስተባባሪነት የገጠር መንገድ ትስስር እና ተደራሽነትን አጠቃላይ አተገባበሩን አስመልክቶ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ እንደሆነ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚ/ዴኤታ ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት ተናግረዋል፡፡

የመሠረተ-ልማት ግንባታ በፈጣን የዕድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አቶ የትምጌታ ገለጸው ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ስለግንባታ ሲታሰብ በጋራ፣ በብቃት፣ በጥራት እና በታማኝነት ለዘላቂ ሀገራዊ እድገት እና ለዜጎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ታሳቢ በማድረግ በትጋት ለሰሩ  ይገባል ብለዋል፡፡

እንደሀገር በሁሉም ክልሎች ሊገነቡ የታሰቡት የገጠር መንገዶች በታቀደላቸው  መሠረት በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ እንዲችሉ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል፡፡

ዛሬን ጨምሮ በቀጣይ ቀናት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የመንገድ ግንባታ ዲዛይነና ስታንዳርድ፣ የግዥ አስተዳደር ፣ የፕሮግራሙ አወቃቀርና አስተዳደር ፣ የአቅም ግንባታ ፣ የፕሮጀክቱን ውጤታማነት ግምገማና የሪፖርት ኦድት ሲሆኑ በአጠቃላይ አንድ ፕሮጅክት ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ የሚያስፈልጉ ሂደቶች በዝርዝር ቀርበው ገለጻና ውይይት እንደሚደረግባቸው በመርሃ ግብሩ ተመልክቷል፡፡

ሪፖርተር፡-ሞገስ ዓሊ

Posted in: News