ሰኔ 15, 2026

አዳማ፣ ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ) በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ በዘመናዊ የኮንስትራክሽን ስራ ላይ ደህንነት እና በካይዘን ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ የህንጻ ስራ ተቋራጮች፣ የሙያ ማህበራትና አማካሪዎች በአዳማ ከተማ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡

የስልጠናው ዓላማም በካይዘን እና አተገባበር ላይ የተሟላ አረዳድ መፍጠር፣ የስራ ባህልን በማሻሻል የሰራተኞች የስራ ተነሳሽነት መጨመር እና በማያቋርጥ የለውጥ ጎዳና ተቋማትን መገንባት እንዲሁም የስራ ላይ ደህንነትን ትኩረት መስጠት እንደሆነ በመድረኩ ተገልጿል።

በካይዘን የልዕቀት ማዕከል አማካሪ እና ተመራማሪ የሆኑት ወ/ሮ ገነት ደበበ የካይዘን ጥልቅ ዕይታን አስመልክተው ካይዘን ማለት የማያቋርጥ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ማምጫ፣ አሳታፊ፣ የበርካታ ጥቃቅን ለውጦች ድምር ውጤት እና ያለ ከፍተኛ መዋለ-ነዋይ የሚሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ካይዘን ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ቴክኖሎጂዎችን፣ የአስተዳደር መመሪያዎችን የአሰራር ሂደት ደረጀዎችን ቀጣይነት እንዲኖራቸው እና በእየ ጊዜው አቅማቸውን ከፍ እንዲል ማሻሻያ ማድረግ እንደሆነ አያይዘው ተናግረዋል።

በካይዘን የልዕቀት ማዕከል አማካሪ እና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ደረጄ አራጌ በበኩላቸው በስራ ቦታ የሚታዩ ብክነቶችን መለየት እና መከላከል በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ገለጻ እንዳሉት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በስራ ሂደት የሚያጋጥሙ አላስፈላጊ ወጪዎችን እና ለስራው ምንም አይነት ዕሴት የማይጨምሩ ነገሮችን ማስወገድ ያስፈልጋል ብለዋል።

በሰራተኛው ላይ የአካል ጉዳት መድረስ፣ በድርጅቱ ላይ የሚከሰቱ የንብረት ውድመቶች እና ስራው ከተጠናቀቀ በዋላ በተጠቃሚው ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ከብክነት መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑ አቶ ደረጄ አክለው ገልጸዋል።

በነገው ዕለትም የስራ ቦታ ማደራጀት እና የስራ ቦታ ደህንነት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና እንደሚሰጥ ከስልጠናው መርሀ ግብር ለመረዳት ተችሏል።

Posted in: ዜና