ሰኔ 15, 2026
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)
የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ ክቡር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በፌዴራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስተባባሪነት በሀገር በቀል ሥራ ተቋራጮች እየተገነቡ የሚገኙ የሦስት ተቋማት የህንጻ ግንባታ ፕሮጀክቶች የደረሱበትን ወቅታዊ ሁኔታ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
ጉብኝት የተደረገባቸው የህንጻ ግንባታዎችም ሠንጋ ተራ አካባቢ የሚገኘውና በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አማካኝነት የሚገነባው የውልና ማስረጃ ባለ 23 ወለል ህንጻ፣ ተክለ ኃይማኖት አካባቢ የተጀመረውና በኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አማካኝነት የተጀመረው ባለ ዘጠኝ ወለል የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ህንጻ ግንባታ እና በሳንታማሪያ ኃ.የተ.የግል ማህበር የሚገነባውና ቦሌ አየር መንገድ የሚገኘው የሲቪል አቪየሽን ባለ ስድስት ወለል ህንጻ ግንባታዎች ናቸው፡፡
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የሦስቱንም የህንጻ ፕሮጀክቶች ወቅታዊ ሁኔታ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸውም ቀደም ሲል በተደረጉ የመስክ ክትትልና ድጋፍ ሥራዎች የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ታሳቢ በማድረግ ከህንጻ ተቋራጮች፣ የፕሮጀክት አማካሪዎች እና የፕሮጀክት አስተባባሪዎች ጋር ተነጋግረዋል በጉብኝቱ ሂደት ሦስቱም አካላት አሉ ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የተሻሉ አማራጮች ናቸው ያሏቸውንና በመንግስት በኩል መደረግ የሚገባቸውን ድጋፎች በመለየት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡
በመጨረሻም ሥራዎች በታሰበው ጊዜ በፍጥነት ተጠናቀው ተቋማቱ በህንጻዎቹ ላይ ገብተው ተገቢውን የህዝብ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉና ከህንጻ ኪራይ ወጪ እንዲታደጉ ለማድረግ ሦስቱም አካላት (ህንጻ ተቋራጮች፣ የፕሮጀክት አማካሪዎች እና የፕሮጀክት አስተባባሪዎች) ተቀናጅተውና ተናበው በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በታሰበው ጊዜ ግንባታዎችን አጠናቆ ለማስረከብ ተቋራጮች በስራው ላይ የሚያሳትፉትን የሰው ኃይል ቁጥር ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸውና የግብአት አቅርቦትን በማሻሻል የሥራ ሰዓትን ማራዘም እንደሚያስፈልግ ገልጸው ወቅቱ የበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያና የክረምት ወቅት መግቢያ በመሆኑ ጊዜን መሻማቱ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ በማሳሰብ ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡