ሚያዝያ 22, 2026
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10/2018፣ (ከመልሚ) በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ዋና አዘጋጅነት እና ከ17 በላይ በሆኑ ተባባሪ አዘጋጆች የተዘጋጀውና የፌዴራል ተቋማትና በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች የተሳተፉበት የመሠረተ ልማትና ኮንስትራክሽን ሳምንት ኤግዚቪሽን እና የፓናል ውይይት “ኢትዮጵያ ትገነባለች! ፈጠራ፣ ፍጥነት እና ጥራት ለመሠረተ-ልማት እመርታ” በሚል መሪ ቃል በትናንትናው ዕለት በክቡር የኢፌዲሪ ም/ጠ/ሚ/ር ተመስገን ጥሩነህ የክብር ዕንግድነት በይፋ ተከፍቶ መጀመሩ ይታወሳል።
ከሚያዝያ 9-12/2018 ዓ.ም በሚቆየው በዚሁ መድረክ ላይ በዛሬው ዕለት የተለያዩ መርሃ ግብሮች የተካሄዱ ሲሆን በጠዋቱ መርሃ-ግብር የመንገድ መሠረተ-ልማትን በተመለከተ ከተማን ከከተማ በማገናኘት የመንገድ ልማት ከመሠረታዊ ተደራሽነት ወደ ፍጥነት መንገድ እያደረገ ያለውን ጉዞ ፤ ከተማን ከገጠር ጋር በማስተሳሰር የሚገነቡ መንገዶች የገጠር ትስስርና ተደራሽነትን ዕውን ለማድረግ ያላቸውን ጠቀሜታ እና የባቡር መሠረተ ልማት ከተማን ከከተማ እና ኢትዮጵያን ከቀጠናው ሀገራት ጋር ለማስተሳሰር እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች የተገኙ ውጤቶች እና እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በቀጣይ ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራትን በተመለከተ የፓናል ውይይት ተካሄዷል።
ይሄን ተከትሎ ዲጅታልና ቴሌኮምን እንዲሁም የኃይል አቅርቦትና የመስኖ ልማትን የተመለከቱ ርዕሰ-ጉዳዮች የፓናል ውይይቱ አካል ነበሩ።
መርሃ- ግብሩ እስከ ሚያዝያ 12/2018 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ነው።