ነሐሴ 17, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23 ቀን፣ 2018 ዓ.ም (ከ.መ.ል.ሚ) የመንግስት የኤሌክቶሮኒክስ ግዥ አፈጻጸምን አስመልክቶ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ለተጠሪ ተቋማት ለግዥና ለፋይናንስ አመራሮች በቀረበ የመነሻ ዳሰሳ ጥናት ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሄዷል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴርና በተባበሩት መንግስታት ፕሮጀክት አገልግሎት ጽ/ቤት (UNOPS) የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን  የመንግስት ግዥ አፈጻጸምን ለማቀላጠፍና የእርዳታ ክትትልና ማስተባባር ማኔጅሜንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም አስመልክቶ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ባለፈው የካቲት 17 ቀን 2026 የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ መሠረት ድርጅቱ ጥናቱን አጥንቶ ለተቋሙ አቅርቧል፡፡

የሚመለከታቸውን የሴክተሩን ሠራተኞች መጠይቅ መነሻነት የዳሰሳ ጥናቱን የመጀመሪያ ረቂቅ ያቀረበው ዴይላይት ኢንተርናሽናል የተባለ  ዓለም አቀፍ ድርጅት  ሲሆን ፣ የሴክተሩን የግዥ ሥርዓት ለማዘመን የሚያስችልና ከዓለም ዓቀፍ የግዥ ስርዓት ጋር የተጣጣመና ተቀባይነት ያለው፣ በመሠረተ-ልማት ዙሪያ የግዥ ችግሮችን የሚፈታ የዳሰሳ ጥናት እንደሆነ በመድረኩ ተብራርቷል፡፡

የዕለቱ የውይይት መድረክ መጠይቆች በሚካሄዱበት ወቅት በጊዜ እጥረት ምክንያት የተቋሙ ሠራተኞች  ምላሽ ሲሰጡ ያላካተቷቸውን ተጨማሪ ግብኣቶችን ለማሰባሰብና የተሟላ ሰነድ አዘጋጅቶ ሥራ ላይ ለማዋል  የተዘጋጀ መድረክ እንደሆነ አማካሪ ቡድኑ  ገልጿል፡፡ 

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በተጠሪ ተቋማት ላይ በተደረገው ጥናት  የመንግሰት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ዓለም ዓቀፋዊ ስታንዳርዶችን ተከትሎ ተወዳዳሪና ግልጽነት የሰፈነበት አሠራር እንዲዘረጋ፣ የነበሩ ክፍተቶች ተለይተው በዝርዝር መቅረባቸው የሚበረታታና ተቀባይነት ያለው ነው ያሉት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር የትምጌታ አስራት(ዶ/ር) የጥናት ሥነ-ዘዴዎችን በመከተል  ሴክተሩ ግዥን በቴክኖሎጂ ታግዞ በመፈጸምና የፋይናንስ አስተዳደርን በተገቢው መንገድ በመምራት መንግስት የሚመድብለትን በጀት ለታለመለት ዓላማ በግልጽነትና በተጠያቂነት የዜጎችን የልማት ጥያቄዎች መመለስ እንዲያስችል ዘመናዊ የግዥ አሠራርን  ዕውን ማድረግ  ከሁሉም አመራርና ባለሙያ የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው  ረቂቅ ጥናቱ በትክክለኛ ባለሙያዎች ተጠንቶ መቅረቡ፣ የ2019 በጀት ዓመትን በምንጀምርበት ወቅት በመሆኑ እና የመንግስት አገልግሎት ሪፎርም ከዝግጅት ምዕራፍ ወደ ትግበራ ምዕራፍ በተሸጋገርንበት ወቅት በመሆኑ፣ እስካሁን የተገኙ ክፍተቶችን እንደተቋም በመፈተሸ ለወደፊቱ  ለላቀ ስኬት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ቅቡልነት ያለው የግዥ አሥራር ስርዓት ለመዘርጋት ተቋሙ ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡

Posted in: ዜና