ሚያዝያ 24, 2026

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ) የሪል እስቴት አልሚዎች ማህበር ከዶርካ ኤቨንትስ ጋር በመተባበር ያዘጋጁትና ከሚያዝያ 15 እስከ 18/2018 ዓ.ም ለአራት ተከታታይ ቀናት በሣይንስ ሙዚዬም የሚካሄደው፣ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው አህጉር አቀፍ የአዲስ አፍሪካ ቀጠናዊ የምስራቅ አፍሪካ ሪል እስቴት አውደ-ርዕይ በዛሬው ዕለት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ክብርት ወ/ሮ ሔለን ደበበ በክብር ዕንግድነት በተገኙበት በይፋ ተከፍቷል፡፡

ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሔለን በመክፈቻ ንግግራቸው ባለፉት 8 የለውጥ ዓመታት የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በተሰሩና ውጤት በታየባቸው ሀገራዊ የልማት ስራዎች እንዲሁም በስራ ዕድል ፈጠራ የኮንስትራክሽንና የሪል እስቴት አልሚዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘርፉ የሚመራበት የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ምክንያት በሪል እስቴት አልሚውና በገዥው መካከል የነበረው ግንኙነት ተአማኒነት የጎደለው እንደነበር የገለጹት ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል አዋጅ አውጥቷል፡፡ አዋጁ የሚመራባቸው ፕሮግራሞች እየተቀረጹ ሲሆን አዋጁ ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ በሚውልበት ጊዜ የአልሚዎች አቅም ጎልብቶ፣ ገዥው መብቱ ተከብሮ በሻጭና ገዥ መካከል መተማመንን የሚፈጥር መልካም ግንኙነት ይኖራል ብለዋል፡፡

አያይዘውም የኢትዮጵያ የሪል እስቴት አልሚዎች ማህበር በተቋቋመ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸው ይህ አውደ-ርዕይ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አልሚዎችን ባሳተፈ መልኩ መዘጋጀቱ መልካም ልምድን ለመቀያየር፤ ዘመናዊ የቤት ልማት እንዲኖር ለማስቻል፣ የዘርፉን ችግሮች በመፍታት የቀደመ ስሙን ለማደስ፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስፋት፣ የሀገር ልማትና የስራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ እና የሀገራችንን የልማትና የለውጥ ጉዞ ለማፋጠን የሚረዳ ስለሆነ ዕውቀቶች፣ ሀብቶች፣ ልምዶች፣ የጋራ ግንዛቤዎች ተደምረው በስራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግ የሚረዳ በመሆኑ አውደ-ርዕዩ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው ብለዋል፡፡ 

በመጨረሻም የማህበሩ አባል ያልሆኑ አካላት ማህበሩን ፈጥነው እንዲቀላቀሉና ሁሉም የዘርፉ ማህበራት አንድነታቸውን በማጠናከር ግንባታዎችን በጥራት፣ በታማኝነት እና በአጭር ጊዜ በማከናወን ዘርፉ ወደላቀ ደረጃ እንዲያድግና በሀገር አቀፍ ደረጃ በአጠረ ጊዜ ለማከናወን በዕቅድ የተያዘውን የቤት ልማት መርሃ-ግብር ዕውን ለማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነታችንን በጋራ እንወጣ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በአውደ-ርዕዩ ላይ ከፍተኛ የዘርፉ የስራ ኃላፊዎች፣ በኢትዮጵያ የቡርኪናፋሶ አምባሳደር፣ የአፍሪካ የሪል እስቴት አልሚዎች ማህበር ዓባላት፣የፋይናንስ ተቋማት፣ የሪል እስቴት አልሚዎች፣ የኮንስትራክሽን ግብአት አቅራቢዎች፣ እና ተጋባዥ ዕንግዶች የተገኙ ሲሆን ከ30 በላይ የሚሆኑ የሪል እስቴት አልሚዎች ያዘጋጁት ኤግዚቪሽን በይፋ ተመርቆ ተከፍቷል፡፡

Posted in: ዜና