መስከረም 4, 2026
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13 ቀን፣ 2018 ዓ.ም (ከመልሚ)የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (JICA) ጋር በአቅም ግንባታ፣ በከተማ ፕላንና በከተሞች የአከታተም ሥርዓት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የስምምነት ፊርማ አካሂዷል፡፡
የስምምነት ፊርማውን ያከናወኑት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፈንታ ደጀን እና በJICA የኢትዮጵያ ዋና ተወካይ ሚስተር ያኩሺ ሂሮዩኪ ናቸው፡፡
የስምምነት ሰነዱን አስመልክተው ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፈንታ ደጀን እንደተናገሩት የኢትዮጵያና የጃፓን መንግስታት ለበርካታ ዓመታት በባህል፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ትስስር የዳበረ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው በቀጣይ አጠቃላይ በከተማ ፕላን ዙሪያ በሚከናወኑ ስራዎች ከJICA አስተባባሪዎች ጋር በትብብር ለመስራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
ድርጅቱ ላለፉት አምሰት ዓመታት የዘርፉን አመራር እና ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የልምድ ልውውጥ በማደረግ እንደሀገር በከተሞች የመረጃ አያያዝን በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራርን ተግባራዊ ለማድረግ መሠራቱን ሚስተር ያኩሺ ሂሮዩኪ ተናግረዋል፡፡