ግንቦት 22, 2026
አዳማ፣ ግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ)
በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ ህዝቡን የመረጃ ባለቤት፣ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ አስተዋጽኦው የጎላ ስለሆነ የህዝብ ግንኙነት መዋቅሩንና የሚዲያ አካሉን የተግባር አንድነትና የመረጃ ፍሰት ለማጠናከር የጋራ መድረክ መፍጠሩ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር የተዘረጋውን የትብብር መንፈስ ከማደሱም በላይ የመረጃ ቅብብሎሹን የተሳለጠ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡
የዘርፉን ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ፎረም በንግግር ያስጀመሩት የሚኒስትር ጽ/አቤት ሀላፊ ተወካይ አቶ በየነ መለሰ እንዳሉት የከተማ ልማት ስራዎች ዘርፈ ብዙ እና እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ ናቸው።
እነዝህን እርስ በርስ ተመጋጋቢ የሆኑ የዘርፉ ስራዎች በተገቢው መንገድ እታች ያለው መዋቅር ድረስ በመናበብ የመረጃ ፍሰት ጠብቆ ተደራሽ ማድረግ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን መዋቅር ዋና ስራ በመሆኑ እንደዚህ አይነት የምክክር ፎረሞች ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብለዋል አቶ በየነ ።
የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ጸጋዬ ሞሼ የቤት ልማት ፖሊሲን አስመልክተው እንደገለጹት ከሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች መካከል አንዱ የመኖሪያ ቤት ወይም የመጠለያ ፍላጎት ነው። ይሄንን ፍላጎት ለማሟላት እና የህብረተሰቡን የቤት ልማት ፍላጎት ጥያቄ ለመመለስ ፓሊስ አስፈላጊ መሆኑ በመንግሥት ስለታመነበት አድስ የቤት ልማት ፓሊስ ጸድቆ ወደ ስራ እንድገባ ተደርጓል።
የፖሊሲው ቁልፍ ውጤት መሰኮች የተመጣጠነ የቤት ፍላጎት እና አቅርቦት፣ የተሻሻለና አስተማማኝ የቤት ግብይት ስርዓት፣ የተሻሻለ የገጠር ቤቶች ደረጃ፣ የጎለበተ ተቋማዊ አቅምና የመረጃ አስተዳደር ስርዓት መሆናቸውን አቶ ጸጋዬ ገልጸዋል።
በቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ የቤቶች ልማት ጥናት እና የግል ሴክተር ተሳትፎ ዴስክ ሃላፊ አቶ ታፈሰ ነጋ በበኩላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ 1388/18 በተመለከተ በዝርዝር አቅርበዋል።
በአዋጁ ማሟላት ስለሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ስምና ዜግነት እንዲሁም ማንነትን የሚገልጽ ህጋዊ ሰነዶች፣ የወንጀል ታሪክ የሌላቸው መሆን፣ የሀገር ሰላም፣ ደህንነት፣ ጸጥታና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የሚያያዝ የክልከላ ገደብ እና መሠል ጉዳዮችን ለፎረሙ ተሳታፊዎች ገለጸዋል።
በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ኢትዮጵያ በደቻ በማጠቃለያው እንደተናገሩት የከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ እስከታች ያለው መዋቅር የሚያካትት ሰፊ እንደ መሆኑ በተገቢው መንገድ መረጃዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ረገድ የሚዲያ እና ኮሙኒከሽን መዋቅር ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል ።
ሀገራዊ የሆኑ የዘርፉ ስራዎችን ተደራሽ የማድረግ ሃላፊነት ስላለብንና በመንግስት (ሚኒስቴር መስሪያ ቤት) የሚወጡ ፖሊስዎች፣ አዋጆች እና ደቦች ተገቢው ትኩረት በመስጠት ለህብረተሰቡ ማስተዋወቅና የሚፈጠሩ ብዥታዋችን ማጥራት እንደምገባ ተናግረዋል አቶ ኢትዮጵያ።
አዲሱ የቤት ልማት ፖሊስ ከፍተኛ የሆነውን የቤት ጥያቄ መመለስ በሚያስችል መልኩ በመንግስት ደረጃ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ተቀረጾ ወደ ስራ የገባ በመሆኑ በቀጣይ ዓመታትም የቤት ልማት ችግሮችን የሚፈታ እና የህዝቡን ጥያቄ የሚመልስ ነው። ወደ ህዝቡ በሚወርድበት ጊዜ ግልጽነት ለመፍጠር በጋራ እንስራ ስሉ ለሚዲያ ተቋማት ጥሪ አቅርበዋል የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚው አቶ ኢትዮጵያ በደቻ።