መስከረም 4, 2026

አዲስ አባባ፣ ነሐሴ 23 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ)  የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር  የከተማ ልማት ፖሊሲ፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ እና የቤት ልማት ፖሊሲ መጽደቃቸውን ተከትሎ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር የሚያስችል የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮች ውይይት አድርገዋል፡፡

ፖሊሲዎቹ በ2030 የኢትዮጵያ ከተሞች ለሀገራዊ እድገትና ብልጽግና ስኬት መሪ ሚና ያላቸው፣ ተወዳዳሪ፣ ዘላቂ፣ ምርታማና ለስራና ለኑሮ ምቹ ሆነው ማየትን ያለሙ ናቸው፡፡

መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፈንታ ደጀን የከተሞች እድገት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን እና ከላይ እስከታች ያለው አመራር ትኩረት ሰጥቶ ከመደገፉ ጋር ተያይዞ ፖሊሲ ማሻሻልና ማዘጋጀት ውጤታማ ስራ ለመስራት ያስችላል ብለዋል፡፡

የከተማ ልማት ፖሊሲ ዓላማው አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ከተሞች ውብና ጽዱ፣ ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻልና የስራ እድል የሚፈጥሩ ከመሆኑም ባሻገር ፈጣን እና ተደራሽ አገልግሎት እንዲኖር የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ ጥናትና ምርምር  ስራ አስፈጻሚ  አማን አሰፋ(ዶ/ር) አዲሱ የከተማ ልማት ፖሊሲ ዓላማ ከተሞች በፕላን የሚመሩ፣ በመሰረተ ልማት የተቀናጁ፣ ቀልጣፋና ዘላቂ ልማት የሚረጋገጥባቸው አካታች ኢኮኖሚና ማህበራዊ ብልጽግና እንዲኖራቸው ማድረግ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ እና የቤት ልማት ፖሊሲ በዝርዝር ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

Posted in: ዜና