ታህሳስ 12, 2025

አዳማ፣ ህዳር 23 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ)

በሀገራችን ከተሞች የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ የተለያዩ የቤት አቅርቦት ስልቶች ተነድፈው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።

በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ በቤት ልማት ፋይናንስ ስርዓት ዝርጋታ ረቂቅ አዋጅ፣ የውጭ ሀገር ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት መብት ለመደንገግ በወጣ አዋጅ እና የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ትግበራ ላይ ከሚመለከታቸው የክልል እና የከተማ አስተዳደር የዘርፉ አመራሮች በተገኙበት በአዳማ ከተማ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።

በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የሚኒስቴር ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አባድር ፋሪስ እንደተናገሩት በዘንድሮው ዓመት መንግስት ለቤት ልማት ግንባታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን በግሉ ዘርፍም የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮች በመጠቀም ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቤት ለሰው ልጅ መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ የቤት ልማት የፋይናንስ በማቋቋም የቤት ግንባታ ለማስቀጠልም እንደ ሀገር እየተሰራ እንደሆነ ሃላፊው አያይዘው ተናግረዋል።

በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የቤት አቅርቦት እና ፋይናንስ ማሻሻያ ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ ሙሉእመቤት ከበደ በበኩላቸው የቤት ልማት ፋይናንስ ስርዓት ዓላማው ጥራት ያለው በቂና ለዜጎች ተደራሽ የሆነ የመኖሪያ ቤት ፋይናንስ በዘላቂነት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን አካባቢያዊ፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ እድገትን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል ።

Posted in: ዜና