ሰኔ 15, 2026

አዳማ፣ ግንቦት 28 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ) በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለህንጻ ስራ ተቋራጮች፣ ለሙያ ማህበራትና ለአማካሪዎች ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቀቀ።

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ ለዘርፉ ተዋናዮች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት በእቅድ አቅዶ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ሙሉዓለም ደበበ እንዳሉት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ሀብት የሚንቀሳቀስበት እና ሰፊ የስራ እድል የሚፈጠርበት እንደመሆኑ መጠን መንግስት እና የግሉ ዘርፍ በጋራ ተቀናጅቶ በመስራት እና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም  የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያስችል እንቅስቃሴ እንዳለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዳታ ማኔጅመንት ሲስተም አጠቃላይ የኮንስትራክሽን መረጃዎችን የሚይዘው በቀጣይ ዓመት ተግባራዊ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ቤቶች ምክትል ቢሮ ሃላፊ ኢንጅነር መኮንን ጥበቡ(ዶ/ር) በበኩላቸው በእያንዳንዱ ግንባታ የሚስተዋሉ ብክነቶች በመለየት ማረም ያስፈልጋል። እንደ አዲስ አበባ ከተማ የወሰን ማስከበር እና የፋይናንስ ችግሮች እየተቀረፉ ነው ብለዋል።

የህንጻ ስራ ተቋራጮች እና የሙያ ማህበራት እንዲጠናከሩ ፕሮጀክቶች ከውጭ ኮንትራክተር ይልቅ ለሀገር ውስጥ ቢሰጥና ከስራው ጋር ተያያዥነት ያላቸው የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ቢሰጡ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል እና ሌሎችም ሀሳቦች ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።

Posted in: ዜና