ጥቅምት 30, 2026

የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴርና የዘርፉ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር የሪፎርም ስራዎች የ2019 በጀት ዓመት፣ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በማኔጅመንት አካላት ተገመገመ፡፡

የተካሄደውን መድረክ የመሩት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ክቡር መሀመድ አብዱራህማን (ኢ/ር) ሲሆኑ የመደበኛ ስራዎች ሪፖርት እና  የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር የሪፎርም ስራዎችን የተመለከተው ሪፖርት  ቀርቧል፡፡

ሪፖርቱ ሀገራዊ አቅጣጫን መሠረት ባደረገና በቀጣይ ሦስት የበጀት ዓመታት የልማት ማዕቀፍ ሆነው እንዲያገለግሉ በተለዩ 6 ስትራቴጂዎች፣ 18 ዋና ዋና ተግባራት እና 136 የውጤት አመላካቾች መነሻነት የተዘጋጀ መሆኑን በመግለጽ የባለፉት 3 ወራትን አፈጻጸም በዝርዝር ቀርቧል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት (ከሐምሌ 1/2018 እስከ መስከረም 30/2019 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት) በዝግጅት ምዕራፍ የተከናወኑ ስራዎችን በተመለከተ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር የሪፎርም ስራዎች ጥናቱ በለያቸው 7 የሪፎርም አምዶችና በሌሎች 2 ጉዳዮች አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ነው፡፡

የማኔጅመንት አካላቱ በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ በመምከር በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ መካተት ባለባቸው ጉዳዮችና በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳብና አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ክቡር ሚኒስትሩ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት፣ ከዕቅድ ዝግጅት ጀምሮ ባለፉት ሦስት ወራት በተከናወኑ ስራዎች በርካታ ተግባራት የተከናወኑ መሆናቸውን ከቀረቡት ሪፖርቶች መረዳታቸውን ገልጸው የቀጣይ ሦስት ወራት ዕቅድን በተለዩት ስትራቴጅክ ግቦች መነሻነት መልሶ ማየትና መከለስ እንደሚገባ ገልጸው በዕቅድ የተያዙ ስራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶና ተቀራርቦ በመስራት ተፈጻሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚሰራና የሪፎርም ስራዎችን በተመለከተም ተቋማዊ አሠራር ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በቅርበት መስራት እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

Posted in: ዜና