ሐምሌ 27, 2026
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ፣ (ከመልሚ) የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የመሠረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ የብራዚል የልዑካን ቡድንን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ የተሰማራባቸውን የመሠረተ-ልማትና የኮንስትራክሽን ዘርፎች በማሳያነት አቅርበዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ ከለውጡ መንግስት ጀምሮ ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ዕድገቱና ለከተማ ልማቱ በሰጠችው ልዩ ትኩረት የግንባታ ዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ የተነቃቃ መሆኑን በማስታወስ ኢትዮጵያ ከመረጠቻቸው 5 የልማት ዘርፎች አንዱ በሆነው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚካተተው የከተማና የመሠረተ-ልማት ዘርፍ ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነና ሀገራችን ኢትዮጵያ የዕድገት ፍላጎቷን ለማሟላት እየተጋች ያለች ሀገር በመሆኗ የልዑካን ቡድኑ በትክክለኛው ሰዓት ላይ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አሁናዊ ፍላጎትና ቢሰማሩባቸው ብለው የገለጿቸው ዘርፎች ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው የቤት ልማትና የመንገድ ዘርፍ ልማቶች መሆናቸውን ገልጸው በኮንስትራክሽን ግብኣቶች ማምረት ዘርፍ ቢሰማሩም ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ይህ ግንኙነት የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች ስላሉ ያሉብንን የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የግብኣት አቅርቦት ችግሮች በጋራ ለመፍታት ተቀራርቦ መስራቱ አዋጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ ዓባላትም በተደረገላቸው አቀባበልና ባደረጉት ፍሬያማ ውይይት መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡