ሚያዝያ 22, 2026
የኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሳምንት “ኢትዮጵያ ትገነባለች፤ ፈጠራ፣ ፍጥነት እና ጥራት ለመሰረተ ልማት እመርታ” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ኤግዚቢሽን እና የፓናል ውይይት በይፋ ተከፍቷል ፡፡
ክብርት ሚኒስትር በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ በኢትዮጵያ ሀገራዊ የልማት ፍላጎትና ዕድገት ላይ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
ኮንስትራክሽን በስራ እድል ፈጠራና መሠረተ ልማት ዝርጋታን ለማሳለጥ ሚናው የጎላ በመሆኑ በመንግስት ልዩ ትኩረት በማግኘት ትልቅ እመርታ እያሳየ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
ሚኒስቴሩ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ልማት ለማሳደግና ቀጣይነት ያለውን መሻሻል ለማረጋገጥ ከዘርፉ የሚነሱ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ልማት፣ እድገትና ስኬት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከኢንዱስትሪው ባህሪ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መውሰድ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
መድረኩ ለኮንስትራክሽን ስራዎች ውጤታማነት በሚያገለግሉ ግብዓቶች ፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት በመለየት የመፍትሄ ሐሳብ ለማቅረብና በመስኩ ያለውን ችግር ለመፍታት እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ ተሞክሮና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማግኘት ያስችላል ነው ያሉት፡፡
ኤግዚቢሽን እና የፓናል ውይይቱ እስከ ሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ይሆናል፡፡