መስከረም 4, 2026
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ) በአዋጅ ቁጥር 1388/2017 የውጭ ሀገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት እንዲሆኑ የተፈቀደ ሲሆን ወደ ትግበራ ለመሸጋገር ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 1147/2018″ ተዘጋጅቶ መጽደቁ ተገልጿ፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በጋራ በአዋጅና በመመሪያ መሰረት የውጪ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ ሰፊ ስራ ስሰራ መቆየቱን የጋራ እና የተናጥል ሃላፊነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ወደ ተግባር ለመግባት ውይይት አድርገዋል፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እንዳሉት የውጭ ሀገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት ማድረግ በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ላይ ምንም አይነት ጫና የማያሳድር እና እንዲሁም የቤት ልማት አቅርቦትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳድግ እና የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ተመራጭነትን እንደምያሳድግ ገልጸዋል፡፡
ለስራው ውጤታማነት የተቋማት ቅንጅትን አስፈላጊ ነው ያሉት ክብርት ሚኒስትር አሁን ላይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራን ወደ ተግባር ምዕራፍ ለመግባት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ፀጋዬ ሞሼ ባደረጉት ገለጻ የውጭ ሀገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት ማድረግ ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሲሆን የቤት ባለቤት ለመሆን መሰረታዊ መስፈርቶችን ማሟላት የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል።