መስከረም 4, 2026
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25/ 2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ) በአረንጓዴ አሻራ፣ በCOP 32 ችግኝ ተከላ፣ የአቅመ-ደካማ ዜጎችን ቤት በማደስና መልሶ ግንባታ በተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ በማዕድ ማጋራት፣ በደም ልገሳ፣ ወጣቶችን በማነቃቃት፣ እንዲሁም በሆስፒታል ለሚገኙ ህሙማን ተደረገ የንጽህና መጠበቂያ ዕቃዎች ድጋፍ እና መሰል የበጎ አድራጎት ስራዎች በ2018 በጀት ዓመት በሚኒስቴር መ/ቤቱና በተጠሪ ተቋማት ትብብር የተሰሩ ስራዎች ጥቅል ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በተመሳሳይ በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር የሪፎርም ስራዎች ላይ ያተኮረው የሪፎርም ጥናት የቅድመ-ዝግጅት ስራና ጥናቱን አጠናቆ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ለመሸጋገር እየተሰሩ ያሉ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች ያሉበት ደረጃ ዝርዝር ሪፖርትም ለውይይት ቀርቧል። የሲስተም ልማትና በዘርፉ ወደ መሶብ አገልግሎት ለመግባት የተለዩ ስራዎችና ያሉበትን ሁኔታ የተመለከተ ሪፖርት ቀርቦ የጋራ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን በመሩትና ክቡራን ሚኒስትር ዴኤታዎችና የሚመለከታቸው የስራ ክፍል ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተሳተፉበት በዚሁ መድረክ ላይ በቀጣይ የጳጉሜ ቀናት የበዓል አከባበርን በተመለከተ ሚኒስቴር መ/ቤታችን ጳጉሜ 2 የማንሰራራት ቀንን ከሌሎች ተቋማት ጋር በትብብርና በቅንጅት ለመስራት ስለሚቻልበት ሁኔታ መረጃዎች ቀርበው የጋራ ግንዛቤ ተይዞባቸዋል፡፡
በመጨረሻም ክቡር አቶ ፈንታ ደጄን በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት የቀረቡት ሪፖርቶችም ሆነ የተሰሩ ስራዎች ውጤት በጥቅሉ ሲታይ ተቋማችን ያለበት የአፈጻጸም ደረጃ ጥሩ የሚባል እንደሆነና ቀሪ ስራዎች በተያዘላቸው ጊዜ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም እስካሁን ድረስ ከተጠሪ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ በመስራት ረገድ ያደረገው ጉዞ ውጤታማ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡