ሐምሌ 1, 2026
ዱከም፣ ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ)
ለሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎቶች ከሆኑት ከምግብና አልባሳት ቀጥሎ መጠለያ አንዱ ነው፡፡ መንግስት መሠረታዊ ፍላጎት የሆነውን የቤት ልማት አቅርቦትን ለማሳደግ በርካታ የቤት ልማት አማራጮችና ቴክኖሎጂዎችን ለማላመድ ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ከእነዚህ ስራዎች መካከል አንዱ የሆነውን የፕሪፋብ ቴክኖሎጂ የቤት ልማት ግንባታን ማፋጠን ደግሞ የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት ያስችላል፡፡ ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ለመጣው የህብረተሰብ ክፍል የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማሻሻል በአጭር ጊዜ ተመርተው የሚገጣጠሙ ቤቶችን መስራት ተገቢ ነው፡፡
በእነዚህ የተገጣጣሚ የህንጻ አካላት የሚገነቡ ቤቶች የሀገር ውስጥ ግብአቶችን በብዛት የሚጠቀሙ፤ ብክነትንና ብክለትን የሚከላከሉ፤ ወጪ ቆጣቢ እና የዜጎችን የመክፈል አቅም ያገናዘቡ ከመሆናቸው ባሻገር ባለሙያዎችን በአጭር ጊዜ አሰልጥኖ ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ መሆናቸው ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡ ከእነዚህ የመፍትሄ አማራጮች አንዱ ደግሞ የፕሪፋብ ቴክኖሎጂ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የኮንስትክሽን ኢንዱስትሪ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ያዘጋጀውና በዱከም ከተማ መግቢያ ላይ በፕሪፋብ ቴክኖሎጂ የተገነባው 48 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት የቤት ግንባታ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
በቅርቡ በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች የተገነባውን የኮሪደር ልማት ተከትሎ የገጠሩን ነዋሪ የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል እየተሰሩ ካሉ ስራዎች መካከል አንዱ በሆነው የገጠር ኮሪደር እየተተገበረ ያለው የፕሪፋበ ቴክኖሎጂ የቤት አሠራር ጥበብ በይበልጥ ከታወቁት በብረት፣ በሲሚንቶ እና በብሎኬት ከሚገነቡ ቤቶች በተለየ በቃጫ፣ በጠጠር፣ በአሸዋ እና በሲሚንቶ ብቻ ተመርቶ የሚገነባው ቤት በቀላሉ ተመርቶ አገልግሎት ላይ ለማዋል የሚቻልበትን ዘዴ ያስተዋወቀ ነው፡፡
ቴክኖሎጂውን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ያላመዱት ኢንጂ.ብርሃኑ ካሣ በጉብኝቱ ሂደት እንደገለጹት ከዛሬ 8 ዓመት በፊት የባለቤትነት መብት ዕውቅና ያገኘው የፕሪፋብ ቴክኖሎጂ በአሁኑ ሰዓት ስታንዳርድ ወጥቶለት በሀገራችን ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች በስፋት እየተተገበረ በመሆኑ የቴክኒክና ሙያ ተማሪዎችን ለማሰልጠን ካሪኩለም ተቀርጾለት ቴክኖሎጂውን በስፋት መጠቀም የሚቻልበትን ዕድል ለማስፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጉብኝቱ ተሳታፊዎች ቴክኖሎጂው በተግባር ተፈትኖ በስፋት እየተሰራበት ያለ በመሆኑ ባዩት ነገር መደሰታቸውን ገልጸው ቴክኖሎጂው እያደገ የሚሄድ በመሆኑ ጅምሩ መስፋት እንዳለበትና በየጊዜው ማሻሻያዎች ሊደረጉበት እንደሚገባ፤ የህንጻ አካሉ የሚመረትበት የተለየ የማምረቻ ቦታ ቢኖረው፤ የላቦራቶሪ ፍተሻ የሚረጋገጥበት ሁኔታ ቢፈጠር፤ የገበያ ትስስር ቢኖር፤ በጋራ አብሮ ለመስራት የሚቻልበት ዕድል ቢፈጠር እና በዘርፉ ከተቋቋሙ ማህበራት ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ቢመቻቹ የሚሉ ምክረ-ሀሳቦችን ለግሰዋል፡፡