ግንቦት 20, 2026
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ) የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒና ክቡር ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ቦሌ ኤርፖርት አካባቢ በመገንባት ላይ የሚገኘውን የሲቪል አቪየሽን
ህንጻ፣ ካዛንቺስ ኡራኤል አካባቢ ያለውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ህንጻ እና አራት ኪሎ ባሻወልዴ ችሎት አካባቢ የሚገኘውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍትሐብሄር ይግባኝ ችሎት ህንጻ ግንባታ ያለበትን ደረጃ በመገምገም በቀደመ የመስክ ምልከታ የተቀመጡ አቅጣጫዎች በምን ያህል ደረጃ ተፈጻሚ እንደሆኑ በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡
በተደረገው የመስክ ክትትል ሦስቱንም ተቋማት ለመገንባት ውል ገብተው እየሰሩ ያሉት የይርጋለም ኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግል ማህበርና ሳንታማሪያ ኮንስትራክሽን ስራውን አጠናቀው ለማስረከብ በገቡት ውል መሰረት የተሰሩ ስራዎችና ያልተጠናቀቁ ስራዎችን በተባለው ጊዜ አጠናቀው ለማስረከብ ያልቻሉባቸውን ምክንያትና በመንግስት በኩል እንዲደረግላቸው የሚፈልጉትን ጉዳይ አንስተዋል፣ በህንጻ ተቋራጮቹና በአማካሪ መሀንዲሶች የቀረበውን ሪፖርት በማዳመጥ ሦስቱም አካላት ተቀናጅተው በመስራት ባጠረ ጊዜ ቀሪ ስራዎች ተጠናቀው ለተፈለገው አገልግሎት ማዋል እንዳለባቸውና በመንግስት በኩል መደረግ የሚገባቸውን ድጋፎች ለማድረግ ዝግጁነቱ እንዳለ በክቡራን ሚኒስትሮች ተገልጾላቸዋል፡፡
ይህ ሲባል ግን በእጃቸው ያለውን ስራ ለማጠናቀቅ ባላቸው ግብአት ተጠቅመው ስራውን በጊዜ የለኝም ስሜት መስራት እንዳለባቸው በማሳሰብ ነው፡፡