ሰኔ 15, 2026

ቢሾፍቱ፣ ግንቦት 27 ቀን፣ 2018 ዓ.ም (ከመልሚ) የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮችና የብቃት ማዕቀፍ ንኡሳን ኮሚቴዎች እንዲሁም የፈደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አመራር በተገኙበት በመንግሰት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የዝግጅት ምእራፍ ስራዎች ተገምግመዋል።

የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ሪፎርሙን አስመልክተው በ11 ወራት ውስጥ በተለያዩ ኮሚቴዎች የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን በእጅጉ አድንቀው እንደተቋም ማከናወን ሲገባ ባልተከናወኑ ቀሪ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበው እስካሁን ያልተፈቱ ተግዳሮቶችን ከተቋሙ የቴክኒክ ኮሚቴና ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በጋራ ተናቦና ተረዳድቶ ለመፍታት ከምንጊዜውም በላይ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በሪፎረሙ አማካኝነት መንግስት የሀገሪቱ ዜጎች የጣሉበትን አደራ በትክክልና በታማኝነት ለመወጣት የድጅታል አሰራር እውን ማድረግ ነው ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ የከተማ ነዋሪዎችን ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ ርካታን በማረጋገጥ ዘላቂነት ያለው ተቋም ገንብቶ ሀገርን ለማሻገር፣ ነጻና ገለልተኛ የሆነ፣ ተጠያቂነት የሰፈነበት፣ ምቹ የሥራ አካባቢን መፍጠር ነው።

በዚህ ሪፎርም ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ለሚገኙ የተቋሙ አመራችና ባለሙያዎች ክብርት ሚኒስትሯ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ሪፎርሙ የተቋም ግንባታ ሀገርንና ትውልድን የሚያሻግር መሆን እንደሚገባው ክብርት ሚኒስትሯ ጠቅሰው ተቋሙ የተለያዩ ዓለማትን የሪፎርም ተሞክሮ በመውሰድ የከተማ ነዋሪዎችን መሠረታዊ ችግር በዘላቂነት የሚፈታ ሪፎርም እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የክትትልና ድጋፍ ቡድን አባላት እንደተናገሩት ተቋሙ ያዘጋጀውን የብቃት ማዕቀፍና የአደረጃጀት የሰነድ ዝግጅት የአባላቱን ትጋትና ብቃት አድንቀው ቀሪ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ አመራሩም ይሁን በጥናት ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ኮሚቴዎች ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ መሠረት ሥራዎች በአስቸኳይ ተጠናቀው ወደተግባር መግባት እንደሚገባ ተናግረዋል።

Posted in: ዜና