ግንቦት 22, 2026
አዳማ፣ ግንቦት 12/2018 ዓ.ም. (ከመልሚ) በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት ጽ/ቤት የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትና የሥራ ፕሮጀክት የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን ከክልል የዘርፉ አመራሮች፣ ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ከተሞች አስተባባሪዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመገምገም ላይ ነው፡፡
መድረኩን በይፋ ያስጀመሩት የከተሞች ምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ብርሃኑ ተሾመ በመክፈቻ ንግግራቸው ሴፍቲኔት ዜጎችን ከድህነትና ከጥገኝነት በማላቀቅ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ተጎጂ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ገበያ በማምጣት ድህነትን በከተማ ለመቀነስ ውጤታማ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየ ውጤታማ የፌዴራል ፕሮጀክት መሆኑን በማስታወስ በከተማ ከሚኖረው 31 ሚሊዮን ከሚሆነው ህዝብ ውስጥ 15 በመቶ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍላችን የደሃ ደሃ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው እስካሁን ድረስ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በፕሮክቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በማያያዝ በዘንድሮው ዓመት በተፈቀደው የ250 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ በጀት ሦስት መቶ አስራ ስምንት ሺህ የአካባቢ ልማት ተጠቃሚዎችን፣ መቶ ሺህ ወጣቶችን፣ ስምንት ሺህ ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ከአፍሪካ ሀገራት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ በመሆኑ በቅርቡ የአንጎላ ልዑካን የኢትዮጵያን ልምድ ለመካፈል መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
የእርሳቸውን የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ በዛሬው ዕለት የጋምቤላ፣ የአፋር፣ የሀረሪ ክልሎች እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የ9 ወራት ዕቅድ የአፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ የጋራ ውይይት የተደረገበት ሲሆን በቀጣይ ቀናት በሚኖሩ መድረኮች የሦስተኛው ሩብ ዓመት የመስክ ክትትልና ድጋፍ ግኝቶች ሪፖርት፣ የገለልተኛ አካል የፕሮጀክት ግዥ የኦዲት ግኝት ሪፖርቶች ቀርበው የጋራ ውይይት በማድረግ የተሻሉ ተሞክሮች የሚሰፉበት፣ ክፍተቶች የሚታረሙበት ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚሰጡበት መድረክ እንደሚሆን የወጣው መርሃ ግብር ያስረዳል፡፡