ግንቦት 28, 2026
ጅግጅጋ ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኢመአ)፦ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የሚታየውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በዘላቂነት ለመቅረፍ ታቅዶ ሲገነባ የቆየው የጅግጅጋ ተለዋጭ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ተጠናቆ በዛሬው ዕለት በይፋ ተመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ፣ የከተማ እና መሠረተ-ልማት ሚንስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር የትምጌታ አሥራት፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር መሃመድ አብዱራህማን (ኢንጅነር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች ፣ የሃገር ሽማግሌዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በበኩላቸው፣ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ለምስራቁ የሀገራችን ክፍል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከማጠናከሩ ባለፈ፣ ማህበራዊ ግንኙነታችንን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ብለዋል አያይዘውም የመሰረተ ልማቱ መጠናቀቅ በቀጣይ ለምናከናውናቸው ታላላቅ ስራዎች ከፍተኛ መነሳሳትን የሚፈጥር ስኬት እንደሆነም ገልጸዋል።
በግንባታው ሂደት ኃላፊነታቸውን በብቃት ለተወጡ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ ያሉ ሲሆን በክልላችን የሚከናወኑ ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችም በተቀመጠላቸው የጥራት ደረጃና የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በአጽኖት ገልጸዋል።”
ዛሬ የምናከብረው የአንድ መንገድ መጠናቀቅን ብቻ አይደለም፤ ዛሬ የምናከብረው የሕዝባችንን የልማት ጥማት የመለሰ፣ የከተማችንን የኢኮኖሚ አቅም ያሳደገ እና የሁለንተናዊ ዕድገታችንን ማሳያ የሆነ ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው ያሉት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚንስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ አያይዘውም ጅግጅጋ የብዙ ባሕሎች፣ የፍቅርና የኢኮኖሚ መገናኛ መሆኗ ይታወቃል። ይህ መንገድ ደግሞ ይሄንን መገናኛ ይበልጥ ያሳለጠና ያቀላጠፈ ያደርገዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሃመድ አብዱራህማን በበኩላቸው፣ የፕሮጀክቱን ጥራትና ደረጃ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ከመንግሥት በተጣለበት አገራዊ አደራ መሰረት የሀገራችንን የመንገድ መሠረተ-ልማት ግንባታ ለማፋጠን እና የሕዝባችንን ተደራሽነት ለማሻሻል የሚያደርገውን ጉዞ ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ይህንን ዘመናዊ መንገድ ተንከባክቦ እና ጠብቆ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ ኃላፊነት ደግሞ የሁላችንም ነው በተለይም ደግሞ የናንተ የነዋሪው ህዝብ ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈውል።
ይህ 7.3 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 30 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሰፊ መንገድ፣ የእግረኛ መሄጃዎችን ጭምር ያካተተ በመሆኑ ለከተማዋ ልዩ ውበትን ሰጥቷታል።
በተለይም ከቶጎ ጫሌ እና ከደገሀቡር የሚመጡ ከባድና ቀላል የጭነት ተሽከርካሪዎች የከተማዋን መሃል ሳያቋርጡ እንዲያልፉ የሚያስችል አማራጭ በመሆኑ፣ በከተማዋ መግቢያና መውጫ ላይ ይታይ የነበረውን አድካሚ የትራፊክ መጨናነቅ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ።
ለግንባታው 672 ሚሊዮን 98 ሺህ 730 ብር ከ28 ሳንቲም ወጪ ሙሉ በሙሉ በፌደራል መንግስት የተሸፈነ ሲሆን፣ ሀገር በቀሉ ይርጋለም ኮንስትራክሽን ግንባታውን ሲያከናውን፣ ኤልዳ እና ዳምራ አማካሪ ድርጅቶች ደግሞ የማማከርና የቁጥጥር ስራውን በጋራ አከናውነዋል።
ፕሮጀክቱ የጅግጅጋን ሁለንተናዊ ዕድገት በማፋጠን ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው በምረቃው ወቅት ተመላክቷል።
መንገዱ ግንባታው ከተጠናቀቀበት ጊዜ ጀምሮ ደረጃውን የጠበቀ የትራፊክ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።