ጥቅምት 30, 2026
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17 ቀን፣ 2019 ዓ.ም(ከመልሚ) የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት የስራ ፕሮጀክት ሀገራዊ የስትሪንግ ኮሚቴ የተጠቃሚዎችን የተሻሻለ ክፍያን መወሰን፣ ፕሮጀክቱን አጠቃላይ ዓላማ ግንዛቤ መፍጠር እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድን አስመልክቶ መደበኛ ስብሰባዉን አካሄዷል፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ሙሐመድ አብድራህማን(ኢ/ር) መንግስት ከአለም ባንክ ጋር በመቀናጀት በ88 የሀገራችን ከተሞች ላይ ተግባራዊ ያደረገው የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትና የሥራ ፕሮጀክት በከተሞቻችን የሚታየውን ድህነት በመቀነስ እና የከተሞችን የጽዳት፣ የውበትና የአነስተኛ መሰረተ ልማት ችግሮችን በማቃለል ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ ፕሮጀክት ሲሆን መንግስታችንም በትኩረት ከሚያስፈጽማቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ብለዋል፡፡
ከተረጂነት አስተሳሰብ በመላቀቅ በዘላቂነት አምራች ዜጋ ለማፍራትና ከድህነት ለመላቀቅ እንደ ሀገር የጀመርነውን ጉዞ መሰረት በማድረግ የፕሮጀክቱ አተገባበር ከዚሁ አንጻር የተቃኘ እንዲሆን በስፋት እየተሰራ ነው ያሉት ኢንጂነር ሙሐመድ በውጤቱም የበርካታ ዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻልና በተጨባጭ ከተረጅነት ወደ አምራችነት መሸጋገር እንደምንችል ያመላከተ ውጤት እየተመዘገበ መመጣቱን ተናግረዋል ፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ የከተሞች ምግብ ዋስትና እና ልማታዊ ሴፍትኔት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተሾመ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ያለፈውን አመት የስራ ሂደት እና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ ለስትሪንግ ኮሚቴ አባላት በዝርዝር አቅርበው ፕሮጀክቱ እንደሀገር ከፍተኛ አካታችነት የሚሰተዋልበት እንደሆነ ገልጸው በተለይ በሁሉም የሀገሪቱ ከተሞች በተመረጡ 88 ከተሞች በፍሐዊነትና በግልጽነት የተለዩ ጾታን፣ ዕድሜን እና አካል ጉዳተኝነትን ታሳቢ በማድረግ ዜጎች በዘላቂነት ኑሮአቸውን ባማሻሻል ከተረጅነት ወደ አምራችነት እየተሸጋገሩ ይገኛሉ ብለዋል ፡፡
የስትሪንግ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በተጨባጭ አካታችነትን ትኩረት በማድረግ ዜጎች ክብራቸውን በሚመጥን ደረጃ ህይወታቸውን በትክክል እየቀየረ መሆኑን በሪፖርት ከሚቀርበዉ ገለጻ ባሻገር ሁሉም የስትሪንግ ኮሚቴው አባላት ወደ ከተሞች በመሄድ ማረጋገጥና የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች በዘላቂነት በጋራ በመፍታት ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይ ስለ ፕሮግራሙ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በማጥራት እና ግልጽ ግንዛቤ በማስጨበጥ የሕዝባችንን ግንዛቤ ልናዳብር ይገባልም ብለዋል የኮሚቴው አባላት ።
በፌደራል ደረጃ ሀገራዊ የስትሪንግ ኮሚቴው አባላት የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የስደተኞችና ከስደት ተመላሽ አገልግሎት ሲሆኑ። በየተቋማቱ አዲስ ለተሾሙ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ስለፕሮጀክቱ አጠቃላይ ገለጻና ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል፡፡
በመጨረሻም የስትሪንግ ኮሚቴ አባላቱ በቀረቡት አጀንዳዎች የተጠቃሚዎችን የተሻሻለውን ክፍያ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ካካሄዱ በኋላ አጀንዳዎቹ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡