GENERAL BACKGROUND GENERAL BACKGROUND
Minimize Maximize

የአሰላ ከተማ ከየት ወዴት የአሰላ ከተማ ከአዲስ አበባ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ 175 ኪሎ ሜትር ርቀት እንዲሁም በሐሳባዊ መስመር 7.58 ደግሪ ሰሜንና 39.07 ዲግሪ ምሥራቅ ከጭላሎ ተራራ ምዕራባዊ ተዳፋት መሬት ላይ ትገኛለች፡፡ በተጨማሪ ከባሕር ወለል በላይ ከ2150-2400 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ ሲሆን በአመዛኙ ወይና ደጋ የአየር ንብረት አላት፡፡ ዶሻ፣ከንቦልቻ፣ሐንቁና ወልኬሣ የተባሉት ጂራቶች የውሃ ጋን ተብሎ ከሚጠራው የጭላሎ ተራራ ተነስተው ከተማዋን በማቋረጥ ወደ ዝዋይ ሐይቅ ይፈሳሉ፡፡ ስለሆነም የአሰላ ከተማ ተስማሚ የአየር ንብረት፣ለም አፈር፣ በቂ የውሃ አገልግሎትና ዝናብ፣ እንዲሁም ለግንባታ ሥራ ሰፊ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ማዕድንና የደን ሀብት አላት፡፡ የአሰላ ከተማ ስያሜዋን ያገኘችው ከጭላሎ ተራራ ምዕራዋዊ ጥግ ጀምሮ ሰፊ ቦታ ላይ ሰፍሮ ይኖር ከነበረው "አሰላ" በመባል ከሚጠራ የአርሲ ጎሣ እንደነበር ከአፈታሪክ እንረዳለን፡፡

አፄ ምኒልክ ከሞቱ በኋላ ልጅ ኢያሱ በትረ መንግስቱን እንደጨበጡ በእሳቸውና በሸዋ መኳንንቶች መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት ሹም ሺር ሲያደርጉ ነጋድረስ ወልደየስ ደሣን በቀድሞው "የአሩሲ" ጠቅላይ ግዛት የግምሩክ መሥሪያቤት አቋቁመው ቀረጥ እንዲሰበስቡ ሲመድቧቸው በ1907 ዓ.ም ወደ አርሲ በመምጣት በዋናው የሐስፓልት መንገድ ከወለኬሣ ወንዝ ድልድይ በስተምዕራብና ከእግዚአብሔርአብ ቤተክርስቲያን በስተሰሜን ችግኝ ጣቢያ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ ኬላ እና ገበያ ማቋቋማቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በሰገሌ ዘመቻ ድል ቀንቶት የተመለሰው የመዕከላዊ መንግሥት ጦር (መሐል ሰፋሪ) ቆንቻ ተብሎ በሚታወቀው ቀበሌና አካባቢ እንዲሰፈር መደረጉ ለወልኬሳ ኬላ መጠናከር እንደ ምክንያት ይቆጠራል፡፡ በሌላ በኩል ነጋድረስ ወልደየስ ደሳ በ1912 ዓ.ም የቀይመስቀል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በሚገኝበት አካባቢ የግምሩክ መሥሪያ ቤት ከመክፈታቸውም በላይ የወልኬሳን ገበያ አሰላ ጤና ጣቢያ ወዳለበት ቦታ እንዲዛወር ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ የወልኬሳ ኬላ የተቋቋመበት መሠረታዊ ዓለማ ከአርሲና ከባሌ ጠቅላይ ግዛቶች ወደ መሐል አገር የሚጓጓዙትን እንደ ማር፣ ቆዳ፣ ሌጦና ሰንጋ የመሳሰሉትን ሸቀጦች ለመቅረጥ፤ በሕግ የታገደውን የባሪያ ፍንገላና ንግድ ለመቆጣጠር ነበር፡፡

Pages: 1  2  3  4  5